አድማስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የዲግሪ እና የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት እና ስልጠና መርኃ-ግብሮች አዲስ አበባ በሚገኙ ካምፓሶች ትምህርታቸውን እና ስልጠናቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ከ3000 በላይ ተማሪዎች በዛሬ ዕለት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በደማቅ ስነ ስርዓት አስመረቀ፡፡

ከዩኒቨርሲቲው ማዕከላዊ ሬጅስትራር እና ፕሮግራሚንግ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በዛሬው ዕለት ከተመረቁ ምሩቃን መካከል 481 በዲግሪ መርኃ-ግብር በአካውንቲንግ፣ በማኔጅመንት፣ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት፣ በኮምፒዩተር ሳይንስ፣ በአይ. ሲ.ቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ሲሆን ቀሪዎቹ ምሩቃን ደግሞ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መርኃግብር ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 4 በተለያዩ የስልጠና ዘርፎች ስልጠናቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው፡፡

ከነዚህ ተማሪዎች ውስጥ ሃያ ስምንቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ ሰልጣኞች ይገኙበታል፡፡

ከማዕከላዊ ሬጅስትራር ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ከአጠቃላይ ተመራቂ ተማሪዎች 72 በመቶው ሴቶች ናቸው፡፡ ይህም ተቋሙ በትምህርት እና ስልጠና ዘርፍ ሴቶችን በስፋት በማሳተፍ አገራችን ለተያያዘቸው የእድገት ጉዞ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሞላ ፀጋይ ለተመራቂ ተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት ዩኒቨርሲቲው እነርሱን ለዛሬው ዕለት አሰልጥኖ በማብቃቱ የሚሰማውን ልባዊ ደስታ ገልፀው ተመራቂዎቹ ከዩኒቨርሲቲው ያገኙትን እውቀት አገራችን ድህነትን ለማጥፋት በምታደርገው የዕለት ተዕለት ትግል ውስጥ በተግባር ሊያውሉት እንደሚገባ ጠቅሰው ከብዙ ውጣ ውረድ በኃላ ለዛሬው ዕለት በመብቃታቸው “እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና ቢሾፍቱ ካምፓስ በዲግሪ እና በቴ/ሙ/ት ስልጠና መራኃ ግብሮች ሲያሰለጥናቸው የቆዩ ከ270 በላይ ሰልጣኞች ነሐሴ 21 ቀን 2008 ዓ.ም ያስመርቃል፡፡

የካምፓሱ ሬጅስትራር ጽ/ቤት እንደገለጸው ከዕጩ ምሩቃኑ መካከል በመጀመሪያ ዲግሪ መርኃ ግብር በአካውንቲንግ እና በማኔጅመንት፣ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መርኃግብር በዳታቤዝ አድሚንስትሬሽን፣በአካውንቲንግ እና በጀት ሰርቪስ ከደረጃ 1-4 ስልጠናቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ናቸው፡፡

በተያያዘ ዜና ዩኒቨርሲቲው በሀርጌሳ ካምፓሱ በመጀመሪያ ዲግሪ መራኃግብሮች ሲያሰለጥናቸው የቆዩ 360 ሰልጣኞች በጳጉሜ ወር 2008 ዓ.ም እንደሚያስመርቅ የደረሰን መረጃ ይጠቁማል፡፡