የአዲስ አበባ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ቢሮ በየዓመቱ በሚያደርገው የሱፐርቪዥንና ኢንስፔክሽን፣ በከተማይቱ ከሚገኙ 75 የግል ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በላቀ አፈጻጸማቸው ለተመረጡ አምስት የአድማስ ዩኒቨርሲቲ ካምፓሶች ዲኖች የምስክር ወረቀትና የገንዘብ ማበረታቻ ሽልማት ተሰጠ፡፡

የማበረታቻ የምስክር ወረቀት ከገንዘብ ሽልማት ጋር የተቀበሉ ዲኖች የመገናኛ፣ የመስቀል፣ የምስራቅ፣ የመካኒሳ እና የቃሊቲ ካምፓስ ዲኖች በቅደም ተከተል አቶ አህመድ ሰይድ፣ አቶ አቡበከር አብዱ፣ አቶ ጥበበሥላሴ ተክለማርያም፣ አቶ አምሳሉ ቶማስ እና አቶ ናትናኤል ስዩም መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲው የቴክኒክና ሙያ ም/ፕሬዚደንት አቶ ብሩ አስማረ ገልጸዋል፡፡

በሽልማት ሥነሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ሽልማቱን ለዲኖቹ በመስጠት ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር ሞላ ፀጋይ በየዓመቱ ለሚደረገው ሱፐርቪዥንና ኢንስፔክሽን ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ ለሌሎች ካምፓሶች ልምድ በማካፈል ሁሉም ካምፓሶች ተመሳሳይ ደረጃ ላይ እንዲገኙ ላደረጋችሁት ጥረት ምስጋና ይገባል ብለዋል፡፡

ፕሬዚደንቱ አያይዘውም በቀጣይም የዓመቱን የምዘና ዕቅድ በማሳካት የእውቅና እድሳትና የምዘና የምስክር ወረቀት ካምፖሶቹ እንዲያገኙ የተጀመሩ ሥራዎችን በከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚወጡ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከተሸላሚዎች መካከል የመገናኛ ካምፓስ ዲን አቶ አህመድ ሰይድ ለፍኖተ አድማስ እንደተናገሩት የማበረታቻ ሽልማቱ የበለጠ ለመስራት እንደሚያግዝ ጠቁመው ይህ ዓይነቱ ማበረታቻ በአድማስ በየዓመቱ ሲፈጸም የነበረ ሲሆን የዘንድሮው ለየት የሚያደርገው በአዲስ አበባ ከሚገኙ የግል ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር ተወዳድረን ባገኘነው ከፍተኛ ውጤት በመሆኑ በጣም አስደሳች ነው ብለዋል፡፡

አቶ አህመድ አያይዘውም ለቀጣይ የተሻለ ሥራ እንዲሰራ ያደርጋል፣ የካምፓሱን ሰራተኞች መምህራንና ተማሪዎችን ብርታትና ጥንካሬ ያጠናክራል፣ ይህንን በቋሚነት እየፈፀሙ ላሉ ኃላፊዎችም ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡