የዩኒቨርሲቲው ቴክኒክና ሙያ ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ብሩ አስማረ ለፍኖተ አድማስ እንዳስታወቁት ቢሮው በአዲስ አበባ መስተዳድር የሚገኙ የግል የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን የትምህርት ጥራትና የሰልጣኝ ተማሪዎች ብቃት ያረጋግጣሉ ያላቸውን የምዘና መስፈርቶች ተጠቅሞ በመገምገም ስደስት ኮሌጆችን በመጀመሪያ ደረጃ የመረጠ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አምስቱ የአድማስ ዩኒቨርሲቲ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ኮሌጆቹ በቅድመ ዝግጅት፣ በትግበራና በድህረ ምረቃ ባላቸው አጠቃላይ እንቅስቃሴና ውጤታማነት መገምገማቸውን የገለጹት ምክትል ፕሬዚደንቱ አምስቱም የአድማስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች የመመዘኛ ነጥቦቹን በተገቢው ሁኔታ በማሟላታቸው ሁሉም መመረጥ ችለዋል፡፡

መስፈርቶቹ የመመሪያና ደንብ አፈጻጸም፣ መረጃ አያያዝ፣ የአሰልጣኞች ብቃት፣ የምዘና ሥርዓትና አተገባበር፣ ተቋማዊ አቅምና በድህረ ምረቃ ያላቸውን የገበያ ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ሲሆን አምስቱም ኮሌጆች በመስፈርቶቹ መሰረት ከፍተኛ ደረጃ መመደባቸውን አቶ ብሩ አስረድተዋል፡፡

ም/ፕሬዚደንቱ አያይዘውም ምንም እንኳን የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይና ሰፊ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ቢሆንም ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን በጀት በመመደብ የኮሌጆቹን አደረጃጀት፣ የትምህርት ግብዓቶችና ብቃት ያላቸውን አሰልጣኞች በማሟላት ለዚህ ውጤት መብቃቱን አክለው ገልጸዋል፡፡

ኮሌጆቹ ለውጤት ያበቃቸውን አጠቃላይ የሥራ ክንውን ወደ ሌሎች የግል ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እንዲስፋፉ ለማገዝም የአዲስ አበባ የቴክኒክና ሙያ ቢሮ ባዘጋጀው የልምድ ልውውጥ ፕሮግራም ከ 75 ኮሌጆች የተውጣጡ አመራሮች ካምፓሶቹን እንዲጎበኙ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በዚሁ መሰረት የመካኒሳና የመገናኛ ኮሌጆች መጎብኘታቸውን የገለጹት አቶ ብሩ ጎብኝዎቹ ያዩትን አጠቃላይ ሁኔታ አድንቀው ተሞክሮውን ወደየተቋማቸው ወስደው ለመተግበር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡

ም/ፕሬዚደንቱ አያይዘውም ተማሪዎች በድህረ ምረቃ ወቅት ሥራ እንዲያገኙ ለማገዝ ዩኒቨርሲቲው የተመራቂ ተማሪዎችና ማህበረሰብ ቢሮ በማቋቋምና በማደራጀት በየዓመቱ በተለያየ የትምህርት መስክ የሚመረቁ ተማሪዎች ከተለያዩ ተቋማት ጋር ግንኙነት በማድረግ እገዛ በማድረግ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡